በለስ አልባ ገነት

Mulugeta Alebachew

Artwork by Vladimír Holina

ዛሬ . . .

ገነቴ በዘመን ኩሽና ውስጥ በእልፍ ዐይነት ወጥ ቤት የተሰራች የሆነ ዐይነት ልዩ ምግብ ሆናለች፡፡ የሆነ . . . የዐረብኛ አሰል ጠብ ብሎበት የኦሮምኛ አሻቦ የላሰ፤ በትግርኛ ባኒ የታጀበ፤ በጣሊያን ደንብ በሹካ የሚበላ በአማርኛ ሳሕን የቀረበ፤ የአፋር የበከል ጥብስ፡፡

መጠሪያዋ በየዘመኑ እየታደሰ፤ አንደበቷም በእልፍ ቋንቋ እየተቀለመ በብዙ ስሞች ውስጥ አልፋለች . . . ገነቴ፣ የጁ፣ ወልድያ (ይሄኛው የሁሉ መገናኛ መሆኗን ያስተዋሉ፤ ከፊንፊኔና ከዚያ በታች ካለው ክፍለ ሀገር የመጡ ኦሮሞዎች፤ የኦቦ ወሎ አባትና አያቶች ያወጡላት ስም ነው)፡፡

እንዲህ አንዱ መጥቶ ሌላው ሲሄድ በዐሥራ ስንትስ ቋንቋና በእልፍ ዐይነት ባሕል የተነቀሰ ጉራማይሌዋን ሸሽጋ እየተሽኮረመመች . . . ከጎንደር በር ደብረ ገሊላ ተዘረጋች . . . ለጥቁር ውሀ ከምትገብረው ሸሊ ወንዝ ትይዩ የሚሄደው ይሄ ጎዳና ሽንጧ ነው . . .

ከደብረ ገሊላ እስከ ቲንፋዝ . . . ጣሊያን ያነጠፈው ቀጭን አስፋልት የካትራሜ ቫስሊን የተቀባ ጥቁር ክንዷ ነው . . .

ከደፋርጌ እስከ ሙጋድ . . . ማንም ሰሞነኛ አሳዳሪዋ ሲመጣ የምታነሳለት መንታ እግሯ ነው . . .

ዐረቦች የመሠረቱት የንግድ መንደር “ሙጋድ” ዳሌዋ ላይ የተሰፋ ኪሷ ነው . . . ከዳሌዋ ከፍ ብሎ . . . የገነቴ አብራክ የመሰለች የሁሉ ማእከል . . . የከተማዬን የጥንት ስሞች አጣምራ የያዘች . . . ኩንስንስ ሰፈሬ የጁ ገነት፡፡

እዚህ ሰፈር በጥቁር ዐይነ እርግብ ሸፍነው መሀል ላይ ቢጥሉኝ፤ በኮቴያቸው ድምፅ ለይቼ አብሮ አደጎቼን ሰላም እያልኩ . . . “ታዲያስ ሠረቀ . . . ዐዲስ ሥዕል አልሠራህም?” . . .

ርቦኝ ሳፋሽክ ስታየኝ ቁራሽ የማትነፍገኝ የሐጂ እንድሪስ ልጅ ሐውለትን እያመሰገንኩ . . . “እግዚሃር ይስጥልኝ ሐውለትዋ” . . .

እንደ ጉድ ወይ እንደ እብድ የሚያየኝን የሰፈር ሰው ጋ ስደርስ ይለይላቸው ብዬ ከልጅነቴ የድቁና ትምህርት በማስታውሰው ግዕዝ አፍ እዘባርቃለሁ . . . “ሰብእ ያዐቢ እምነ አራዊት ወእንሰሳት?”

አልፌያቸው ስሄድም ከንፈር መጠጣቸው እያሳቀኝ . . . “እናንተ የገነቴ ቆንጆና ቆነጃጅት ሆይ . . . መልካም ከንፈራችሁን ለራሳችሁ እንጂ ለእኔ አትምጠጡ” እያልኩ . . .

ኩሊ አስፈልጓቸው ሶሻሊስታዊ ቀለሙ ያልጠገገ የሥራ መደቤን በጩኸት ለሚጠሩ . . . (“ወዛደር! ወዛደር!”) ትሁት እሺታዬን እያሰማሁ . . .

መንገድ የሳቱ ዐይነ ስውራንን መርቼ ምርቃት እያፈስኩ ሁሉ . . . “ከዘመን መቅሰፍት ይሰውርህ፤ ከፍሎ ከመውጣት ያድንህ ልጄ!” እየተባልኩ . . .

ምንም ሳልቸገር፤ እጄን ኪሴ ከትቼ፤ “እሪኩም ዘመዳ”ን እያፏጨሁ፤ ወደ ቤቴ ወይ ዘወትር ወደምገኝባት ዐይዳ ዳቦ ጋ ያለች የኡላጋ ዛፍ ሥር በሰላም ለመድረስ እችላለሁ ብል አላጋነንኩም፡፡

 
*

ትዝታ፤ ኑሮና እውቀቴ እዚህ መንደር ነው . . . ትናንቴ፤ ዛሬና ተገማች ነገዬም ጎዳናው ላይ ነው፡፡ “ቤቴ” ስል በመንግሥት ቤቶች መካከል ያለች ዛኒጋባዬን ብቻ አይደለም፡፡ ሽንቁር የበዛበት መዝጊያው ድንበር ሊሆንልኝ አይችልም፡፡ ቤቴ ጎዳናውንም ይጨምራል፡፡ ቤቴ ሌሎች ቤቶችንም ይጨምራል፡፡ ቤቴ ሰፈሩንም ያጠቃልላል፡፡ ቤቴ ከተማውንም ያካትታል . . .

እዚች ከተማ ውስጥ . . . በቅንጭብና በአረግሬሳ፤ በዕንጨትና በግንብ፤ በቆርቆሮና በአየር በታጠሩ ቤቶች መካከል በተጋደሙ ንዑሳን ጎዳናዎች ላይ ብዙ ዕውቀትን ልክ እንደ ጠጠር ከመንገድ ዳር የለቀምነው ትዝ ይለኛል፡፡ እምነትና ክህደትን፤ ወገንና ማንነትን፤ እኛ እና እነሱን በየሰፈራችን የተማርነውን አስታውሳለሁ፡፡

ይሄው ጎጠኛ ዕውቀታችን ባነሳሳው አድሬናሊን በጉርምስና ዘመን ጎራ ለይተን ዱላ ስንማዘዝ “ደፋርጌ እንጂ ደፋር አይደላችሁም” ብለን የገመትናቸው መወለዳችንን እስክናማርር ሲወቅጡን፤ ሌላም ጊዜ ስንቀጠቅጣቸው . . .

በቡሄ ጅራፍ ግርፊያ፤ የአገራችን ልጆች የሰው ወገን እንዳልሆኑ ሁሉ ቁጋችን ላይ ቶፓዝ አስረን የጉባ-ላፍቶ አቻዎቻችንን ገላ ተልትለን . . . ፊታቸውን ደም ያለበሰው ያ ደም የእኛም መሆኑን ልብ ሳንል . . . ምላሳችን በአፋችንን እንደቀረጠፍን ሳይገባን በድል አድራጊነት የተምነሸነሽነው . . .

እዚህ ሰፈር ውስጥ፤ “የልጅነቴ አበባ እርግፍ ትበል” ብለን ምኑንም ሳናውቀው ዐዋቂዎች ሲሰሙን በሚያስደነግጥ አባባል ተማምለናል . . . መሐላችን በሐሰት ነበር መሰለኝ አበቦቻችን በልጅነታችን ረግፈው ይሄው ፍሬ አልባ መሆናችንን ሳስተውል “ከዘመን መቅሰፍት ይሰውራችሁ፤ ከፍሎ ከመውጣት ያድናችሁ!” ብለው የመረቁን ሀሉ የለበጣ መሰለኝ፡፡


*

ዳሩ ተቀምጬ የምውልበት መንገድ ፒስታ ነው፡፡ ቀበሌውና ማዘጋጃ ቤቱ እንደ እባብ ካብ ለካብ እየተያዩ በአንተ ትብስ አንቺ ትብስ ከሃላፊነት ሲሸሹ ስንት ዘመን ወሬ ይናፈሳል፡ “በቃ በዚህ ዓመት አስፋልት ሊደረግ ነው”፡፡ የፉክክር አስፋልት ሳይነጠፍ ያድራል . . . ክረምት መጣሁ ሲል፤ ሁለት ሦስት መኪና ያልተጣራ ወርቅ የመሰለ ቢጫ አፈር ደፍተው . . . በቡልዶዘር ይደለድሉታል፡፡ ጓል ድንጋዮቹ በብረት መጋፊያው እየተገፉ ወደ ዳር ወጥተው የጎዳናውን ጠርዝ ይከትራሉ፡፡

አፈር ይቅለላትና እናቴ ያኔ ኪቢቃሎ ሰፈር ሚካኤል ቤተክርስቲያን ጎን ቤት እሰራለሁ ብላ ጀምራ . . . አሁን ድረስ ከመሰረቱ የወጣ ጅምር ቤት የሚጨርሰው አጥቶ የዱርዮች ኩስ መጣያ ሆኖ አለ . . . ለእሱ ውሀ ልክ ማሰሪያ እንዲሆናት ድንጋዮቹን እየለቀምን እንድንሰበስብ አድርጋን ነበር፡፡

ከአገር ሀብት የድርሻችንን ለመውሰድ የመጀመሪያውን ድንጋይ በማንሳት ያሟሸነው እዚህ ሰፈር ነው . . . የሕዝቡን ጠጠር ከመልቀም የሕዝቡን ሳንቲም ወደ መልቀም መሄዳችን ከድንጋይ ዘመን ወደ ብረት ዘመን ያደረግነው ፈጣን የስልጣኔ ሽግግራችን ነው፡፡ እህስ ጆንትራው! አበባችን በሞሳነታችን አልረገፈም?
 

*

ከዩኒቨርሲቲ ተባርሬ ድብርቴን ለማራገፍ . . . የናፈቀኝን የሰፈሬን አየር በመስገብገብ ልተነፍስ የሳንባዬን ክንፎች ዘርግቼ ስወጣ . . . አብሮ አደጎቼ የነበሩ የሰፈሬ ልጆች ዘር እየቆጠሩ እንደ ካርታ ሥራዎች ድርጅት ድንበር ሲያበጁ ደረስኩ፡፡

ሸሸኋቸው፡፡

መውደዳቸውን በመልበስ ተስፋ ተጠምዳ የተራቆተች ንፁህ ልቤን በሸማ ልሸፍን በከንቱ እየለፋሁ ራቅኳቸው፡፡ መለመላዋን በቀረች ልቤ ሳቁ፡፡ ከግንቦት ልደታ ቆሌ አፍ ነጥቀን፤ በጋራ ጠብሰን ከበላነው የነጭ ጠቦት ደም ይበልጥ የሚጎትት ሌላ የደም ልጓም አለ አሉኝ፡፡ ረመጥ ላይ አፈንድተን ከበላናቸው መንታ የበግ ቆለጦች፤ እሾኩን በአፈር አራግፈን እየተጎራረስን ከሰለቀጥነው የትግሬ ሙዝ የላቀ፤ ዛፎች በጥተን ከመጠጥነው ወለላ በላይ የሚያስተሳሥር ዘር አለ ተባልኩ፡፡ እስካሁን ጭንቅላቴን በመገረም እነቀንቃለሁ፡፡

ዋጋ ከፍለን ወደምንወጣበት ገደል ተወርውረን ለመግባት በቋፍ ላይ አይደለንም? ከዘመን መቅሰፍት ለመሰወርስ አልታደልንም?


*

አብሮ አደጌ፤ ወዳጄ ልቤ በዛብህ ኀብተአብ ከአባቱ ጋር አገር ለቅቆ እስኪሄድ ማን ትግሬ ማን ኤርትራዊ እንደነበር አላውቅም ነበር፡፡ እትዬ ሀዳስ ከምፅዋ ባዶ እጃቸውን ሲመጡ፤ የመረተ አክስት ወይዘሮ መዘንግእም ከአገር ተባርረው እዮሲያስ ከሚባል መልቲ ልጃቸው ጋር ወደ አስመራ ሲሄዱ . . . ጉቦ አጉርሰው፤ በዘመድ አስለምነው የቀሩት እዚሁ ሲቆዩ ግን . . . እዚችው ኡላጋዬ ሥር . . . በተበሳሳ ጥላዋ ተከልዬ ላውቀው የማልፈልገውን ሁሉ ከአስፈላጊው ዕውቀት ቀላቅዬ ተማርኩ . . . የትዝታዬንም እንጀራ ጣፋጩን ከመራሩ ጋር ደባልቄ ጋገርኩ . . .

. . . ይሄንና ያን. . . ሰው መሆንን የሚያስረሳ፤ ወንድማማችነትን ቆርጦ የሚጥል ምን ዐይነት ሰይጣን የሞረደው፤ እንዴት የተባ ካራ ነው ፖለቲካ?