from ዳኛዉ ማነዉ?

ታደለች ኃ/ሚካኤል

Tadelech Hailemikael

Artwork by Genevieve Leong

በአንደኛዉ ቀን በመግራፊያዎቹ ክፍሎች ትይዩ ኮሪዶሩ ዉስጥ መርማሪዉ ተኮላ አስቆመኝ። ሌላ የሚገረፍ ሰዉ መኖሩን ያወቅኩት በጣም አስፈሪ የታፈነ ድምፅ ስሰማ ነዉ። አዉቆ ነዉ እዚያ ያስቆመኝ። ብዙ ጊዜ ያደርጉታል። እኔንም አንደኛዉ የሚገማ ምርመራ ክፍል እየነዳ አስገባኝ።  

የመግረፊያዉ ክፍል እርጥበትና የሽንት ሽታ ያጥወለዉላል። ዘቅዝቆ ሊሰቅለኝ ሲጣደፍ አስተዋልኩ። በዚህን ጊዜ ነበር አንድ እሁድ ዶክተር ካሳሁን መከተ ማእከላዊ ሰባት ቁጥር በፍርግርጉ በኩል ተንጠራርቶ ያወራልንን ያስታወስኩት።

ያንን የባላገር ፈትል ቀሚስና ነጠላ ለብሰሽ ሲያመጡሽ ዘመዶቼን ከጭልጋ ያመⶏቸዉ መስሎኝ ደንግጬ ነበር እያለ ብዙ ስናወራ ቆየን። በሇላ ወደክፍሉ ሊገባ ሲል እንዲያዉ “እርጉዝ ብትሆኑ ጥሩ ነበር” አለ። ምክንያቱን ስንጠይቀዉ “ዳሮ የተባለችዉ የብርሃንና ሰላም የሰራተኞች ማህበር የስራ አስኪያጅ አባል የዘጠኝ ወር እርጉዝ ከተገደለች በሇላ በዉስጥ ሰርኩላር እርጉዝ ሴቶች እንዳይገደሉና እዳይገረፉ ታⶋል” አለን። ከሄደ በሇላ ሁለታችንም (እኔና መኪያ) ተጠያይቀን ብዙም አልገፋንበትም።  

የዚያን እለት መሰለና ተኮላ የተባሉት መርማሪዎች ሲያጣድፉኝና ገልብጠዉ ሊገርፉኝ ሲሰናዱ የዶክተር ካሳሁን አበባል ትዝ አለኝ። ቆሻሻዋን የካልሲ ኯስ አፌ ዉስጥ ሊጠቀጥቅ ሲዘጋጅ “እርጉዝ ነኝ” በሇላ ለምን አልተናገርሽም እንዳልባል! በማለት ባለመናገሬ የሚያስጠይቀኝ ይመስል አስጠነቀቅኯቸዉ።  እነሱም ወዲያዉ ደንግጠዉ ከድርጊታቸዉ ቢታቀቡም እዚያዉ እንዳንጠለጠሉኝ “ያረገሽ እንደሆን ታዲያ ንጉስ ያረገሽ መለለሽ? እያሉ ተሳለቁብኝ። እንዳሰበዉ መግረፉን ሊቀል እንድማይችል ግን ገባኝ። ሳያወርደኝ ጥሎኝ ሄደ። ምን ያህል እንደቆየ አላዉቅም። በዚያ ሁኔታ ደሜ ሁሉ ወደጉሮሮዬ እየመጣ አንገቴ የወፈረ መሰለኝ። ትንፋሽ አጠረኝ። ተስፋ በመቁረጥ ላይ እያለሁ በድንገት በሩ ድርግድ አለና “አዉርዳት! አዉርዳት! ተባለ። አዉርዶኝ ስቆም የምርመራዉ ክፍል ሃላፊ የሚባሉት ኮሎኔል (በሇላም ጀነራል) ለገሰ በላይነህ ነበሩ። እኚህ ሰዉ መጀመሪያ ማእከላዊ የገባን እለት አንዱ አላዋቂ ወታደር ስለአይሮፕላኑ ሲጠይቀኝ የተቆጡት ሰዉ እንደሆኑ ወዲያዉ ገባኝ።

“እህ ታደለች እርጉዝ ነኝ ነዉ የምትይዉ? ለመሆኑ ከማን ነዉ?” ሲሉ ጠየቁኝ። ምን ማለት ፈልገዉ እንደሆነ ባይገባኝም “ከባሌ ከብርሃነመስቀል ነዋ” በመለት መለስኩላቸዉ። ጊዜም አላጠፉ ሁለት የታጠቁ ወታደሮችና ተኮላ አጅበዉኝ ቤላ ኃይለስላሴ ወደተባለዉ ሆስፒታል ወሰዱኝ።

እንደደረስን የእርግዝና ምርመራ እደሆነ ተኮላ ነግⶂቸዉ መሰለኝ ነርⶃ ይዛኝ አንድ ክፍል ስትገባ ወታደሩም ተከትሎ በር ላይ ቆመ። ሽንት ሰጥቼ በሁለቱ ወታደሮች መሃል ኩስስ ብዬ ቆሜያለሁ። እርጉዝ ባልሆን ምን ሊደርስብኝ እንደሚችል እያሰብኩ፤ “አምላኬ ብቻ የዛሬን አዉጣኝ!” እያልኩ ስጨነቅ ነበር ነርⶃ ከኮሪደሩ ጫፍ ጀምራ “እርጉዝ ናት! እርጉዝ ናት! እያለች የመጣችዉ። እርⶃም እርጉዝ ባልሆን ምን ሊደርስብኝ እንደሚችል ያወቀች ይመስል!  አምላኬን በልቤ አመስግኜ እፎይ አልኩ። በዚህም የተነሳ በተከታታይ በተደረገብኝ ምርመራ ሊደርድስብኝ የነበረዉ ግርፋትና ውፌ ይላላ ቀረልኝ።

‘ብርሃነመስቀል የት ነዉ? አሁን አንድ ሃይል ከአንቺ ጋር ይሄዳል። ትመሪናለሽ!’ የሚል ነዉ የዘወትር ጥያቄያቸዉ።

‘በመጀመሪያ ተዘዋዋሪ ናቸዉ። አንድ ቀን የዋሉበት አያድሩም። የት ብዬ ነዉ የምወስዳችሁ? አልችልም። የሚደርሱበትን አላዉቅ’ እያልኩ የሌለ ነገር እየተናገርኩ እምቢታዬን ስገልፅ ሰነበትኩ። 

በዚህ ዕለት ከምሳ በሇላ መርማሪ መቶ አለቃ ከበደ ከእስር ቤት ወስዶ ምርመራዉ ክፍል በማስቀመጥ በሃዘን እየተመለከተኝ “ይኸዉልሽ ብልጥ ሁኚ፤ ዝም ልልሽ አልችልም። አላዉቅም እያልሽ እምቢታሽን ብቻ ከመግለፅ በሌላ ዘዴ ለመመልስ ሞክሪ” አለና መከረኝ። በዚህን ጊዜ አንደበቴን ገርቼ፤ ድርቅ ብሎ እምቢ፤ አልችልም የሚሉትን አነጋገር ትቼ በመለሳለስ “አሳያችሁ ነበር ግን አንድ ቦታ አይቀመጡም። ምስራቅ ይዣችሁ ብሄድ ወደ ምእራብ ሄደዉ ሊሆን ይችላል። ደቡብ ሲባል ሰሜን ሊሆኑ ይችላሉ። በዚያ ላይ ስጥር ዉስጥ አንድ ሰዉ እንኯ ተደብቆ ቢያጠቃን ምን ይባላል? እያልኩ የስነ ልቡና ጦርነት አከል ምላሽ ሰጥሁ።    

በአንድ ማህበር፤ በአንድ ተቇም ተመሳሳይ ስራና ደምወዝ የሚከፈላቸዉ ሆነዉ ሳለ ለምንድን ይሆን አንዳንዶቹ ፍፁም አዉሬ፤ አንዳዶቹ ደግሞ በአዉሬ መሃል የተገኙ ሰዎች ሆነዉ የሚታዩት? እንደዚያ አዉሬ እንዲሆኑ የሚያደርግ ምን አይነት ህሊና ይሆን? ይህን ሁኔታ ከላይ የጠቅስኯቸዉ ሁለት አይነት መርማሪዎች ላይ ይስተዋልኩት ነዉ።

እነዚህ ሁለት ዓይነት አዎች እንዴት በአንድ ተቇም ተገኙ? አንድ ሰዉ እምነቱ የራሱ ነዉ። እምነቱን ከስራዉ ጋር ማቆራኘት ያለበት አይመስለኝም። መርማሪዎቹ የሚከፈላቸዉ ለምርመራ ስራቸዉ ነዉ። ‘እምነትና አስተሳሰባቸዉ ምንም ቢሆን ከተሰጣቸዉ ስራና ሃላፊነት አልፈዉ ሲያጠፉ ለምንድን ነዉ የማይጠየቁት?’ ብለን ልንጠይቅ ግድ ይለናል።

እርግጥ መፈራረጅ ልዩነት አግዝፎ፤ ስም የማጠልሸት ተግባር ዉስጥ ይካተታል። እኛና እነሱ በሚል፤ በአስተሳሰብ በአⶈⶈር በማንነት ተከፋፍሎ እስከ መጠፋፋት ያደርሳል። በኛ ዘመን የሆነዉና የተተገበረዉ ይህ አይነቱ ክስተት ነበር።

በዚያን ወቅት ስልጣን በያዘዉ መንግስት ለብዙ ጊዜ መሰል መፈራርጅን በስፋት መተግበሩ ተስተዉⶀል። እንደ አንድ መንግስት ዜጎቹን መዳኘት ትቶ እራሱ ተዋናይ መሆኑ ሃላፊነቱን ለመዘንጋቱ ምስክር ነዉ። ይህ ሁኔታ የብዛም ይነስም፤ በሁሉም በአብዮቱ ዘመን በነበሩት ትዉልዶችም መካከል ተክስቶ መፈራረጅ ለመጠፋፋት ዳርጏቸዋል።

ከሁሉም በላይ ግን የነበዉ መንግስት ዜጎቹን እደመታደግ እስከ መጨረሻ የስልጣን ዘመኑ ድረስ ይህን ድርጊት በተለያየ ደረጃ ሲፈፅመዉ ተስተዉⶀል። ‘ዳኝነት ሆይ ከወዴት ነሽ? ስንል የቃተትነዉ በዚህ የተነሳ ነዉ።

የብረሃነመስቀል መያዝ

በመንዝ የሚገኘዉ የእርማት ንቅናቄዉ ከእለትለት ችግሮች እንደገጠሙት፤ በነመንግስቴ ደፋር በኩልም የሚደርሰዉ ጫና መበርታቱ ግልፅ እየሆነ መጥⶆል። እንዲያም ሆኖ ግን የአዲስ አበባዉ የእርማት ንቅናቄ ቡድን ዉሳኔ ትግሉ ተጠናክሮ ይቀጥል የሚል ሆነ።  ለዚህም የሰዉ ሃይል፤ የቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ በእርገጠኝነት እንደሚያቀርቡ ገለፁ።  ንቅናቄዉ መንታ መንገድ ላይ የመገኘቱ ጉዳይ ለሁላችንም ግልፅ ነበር። በተቻለ መጠን ከነመንግስቴ ደፋር ተለይቶ ወደ ሰሜን ለመጏዝም እቅድ ወጣ። ይህን ለማድረግ እንዲቻል የመንገድ ቅኝትና መልእክትም ሊያደርስ የሚችል ሰዉ እኔም ከመነሳቴ በፊት ቀድም ብሎ ተልኯል።

መስቀለኛ መንገዱን ለመሻገር ጠንካራዎችና ቁርጠኛ የሆኑት ብቻ እንዲቀሩና ከተማ ዉስጥ ለአደጋ የተጋልጡም ወደ ሜዳ እንዲመጡ ተወሰነ። እኔም ወደ ዉጪ ሄጄ እንድሰራ የተደረገዉ ከዚሁ ዉሳኔ ጋር በተያያዘ ነዉ። በዉሳኔዉ መሰረት የአዲስ አበባዉ ቡድን መሳሪያ፤ ቁሳቁስና የሰዉ ሀይል በመያዝ ወደ መንዝ ተንቀሳቀሰ። ሆኖም ከአዲስ አበባ የተነሱት በቀጠሮ ሰአት ለመድረስ ባለመቻላቸዉ ከሜዳ ሊቀበላቸዉ ከመጣዉ ሀይል ጋ ሳይገናኙ ቀሩ። በዚህን ጊዜ የአዲስ አበባዉ ቡድን መሪ ጌታቸዉ ስዩም ከራሱ ጋ ሶስት ሆኖ ቀደም ብሎ ወደሚያዉቀዉና ሰራዊቱ ወዳለበት በመሄድ እነ ብርሃነ መስቀልን ተገናኘ።   ሌሎቹ ኤእዛዉ ቆይተዉ ኤእንዲጠብቁ ትእዛዝ ሲተላለፍ መሳሪያዉንም ጏ ሳ ላይ ቀብረዉታል። በዚያዉ ቀን ምሽትም አንድ ሃይል ይዘዉ መሳሪያዎች ወደተቀበሩበት ሄደዉ አዉጥትዉ ወሰዱ። ሆኖም እዚያዉ እንደሚጠብቇቸዉ ያሰቡትን አባላት ግን ሳያገⶉቸዉ ቀሩ። እነዚንም አባላት በዚያዉ ጊዜ የመኪና አደጋ የገጠማቸዉ ናቸዉ። እኔም ተመልሼ መንገድ እንዳሳያቸዉና ከነ ብርሃነ ጋ እንዳገናኛቸዉ ከጉዞ እቅዴ በተቃራኒ ተመልሼ የሄድኩበት በነሱዉ ምክንያር ነበር። ከላይ እንደተጠቀሰዉ በመንገድ ላይ ለመያዝ በቃን።  

ይህም መረጃ መንግስት በእርማት ንቅናቄዉ ላይ የበለጠ ትኩረት እንዲሰጥ አደረገዉ። ሃይሉን በማጠናከርም ለሁለት ወራት ያህል የማያባራ አሰሳ በመንዝና አጎራባች አካባቢዎች አድርጎ ከወራቶች በሇላ ከበባ ዉስጥ አስገባቸዉ። በዚህ የተጠናከረ የአሰሳ ዘመቻ በአጠቃላይ በአካባቢዉ የነበሩ ታጣቂ ቡድኖች በሙሉ በቁጥጥር ስር ማዋል ችⶀል።

በጥምና በረሃብ የተንገላታዉ ሃይል አረፍ የሚልበት ዋሻ ድረስ ገስግሰዉ የተባለዉ ሰርጎገብ ወታደሩን እየመራ በመምጣት፤ እንደተከበቡ በመግለፅ እጅ እንዲሰጡ በድምፅ ማጉያ ጠየቀ። 

ሰራዊቱም በዋሻ ዉስጥ ምክክር አደረገ። በመርህ ደረጃ የምንቀበለዉ፤ “ከማይመጣጠን ግዙፍ ሃይል ጋር በመጋፈጥ አደጋ ዉስጥ ከመግባትና ሁሉንም ከማስጨረስ ይልቅ ሊተርፉ የሚችሉትን አባሎች ማሰብ ተገቢ ነዉ” የሚል ነበር። በመሆኑም እዚያ የነበሩት ተመካክረዉ አንድ ሁለቱ እንታኮስ ቢሉም አብዛኛዉ እጅ መስጠቱን መረጠ። በዚህን ጊዜ ብርሃነና ትስፋ ወጥተዉ በሰላም እጃቸዉን መስጠት እንደሚፈልጉና አለቃቸዉን እንዲያገናኙኣቸዉ ጠየቁ። በጠየቁት መሰረት ሃላፊዉ መጥቶ መረከብ ያለበትን ተረክቦ በዚያኑ ቀን በሄሊኮፕተር ወደ አዲስ አበባ መጡ። 

ብርሃነመስቀል ዉስን አባላትን የያዘ ጠንሳሽ ጦር እራሱን በመከላከል መቆየት እንጂ፤ ዝም ብሎ መጋፈጥ እንድሌለበት አዘዉትሮ ይናገር ነበር። በዚህም የተነሳ በህይወት ሊተርፉ የሚችሉትን አባላት በማሰብ፤ “እኛ አጥፍቶ የማጥፋት ዓላማ የለንም” በማለት አብረዉት የነበሩትን ጎዶች ለማዳን ችⶀል። ከእርሱ ጋር ከተያዙ አብዛኛዎቹም በእስር አሳልፈዉ አሁን በህይወት መገኘታቸዉ አርቆ አሳቢነቱን አመልካች አድርጌ እወስደዋለሁ።

ብርሃነመስቀል በደርግ ተይዞ ምህረት አገኛለሁ የሚል እምነት አልነበረዉም። ቢሆንም ግን እርማት ንቅነቄዉ የሚያምንበትን ዓላማ በግልፅ ለማሳወቅ ከመጠጣር አልታቀበም። የዲሞክራሲ ማእከላዊነት መርህና የፓርቲ ዲስፕሊን በማክበር ከፓርቲዉ ማእከላዊ ኮሚቲ እስኪታገድ ዝም ብሎ ቢቆይም፤ በኢህአፓ ክሊክ የተነፈገዉን ድምፅ ማሰማት ችⶀል። ለዚህም ምስክር ይሆነን ዘንድ እዉነትን ማወቅ ለሚፈልጉ የሚሆን ታሪካዊ ሰነድ ትቶልን አልፍዖል ።

ሽማግሌዉ በማእከላዊ

እድሜ ቇንቇ ነዉ። አንዳንዶች ይኖሩታል፤ አንዳንዶች ደግሞ ስባም፤ ሰማንያም ከዛም በላይ ይኖሩታል እንጅ መኖራቸዉ ምንም ቇንቇ አይኖረዉም።   ሌሎች ደግሞ የሚኖሩት ለትንሽ ጊዜ ነዉ በሃያዎች በሰላሳዎችም ይሞታሉ። የተናገሩት ያሰቡት ያለሙት የኖሩት ቇንቇቸዉ ከዕድሜያቸዉ ልቆ ለዘመናት ይዘልቃል።

ሽማግሌዉ ሲሞት አራት አስርቶችን እንኯን አልኖረም። “በወጣትነት ዕድሜዉ ምን ሆኖ ነዉ የሸመገልዉ?” ይህን ያሉት በማዕከላዊ እስር ቤት ታስረዉ የነበሩት ፋርማሲስት መኮንን ናቸዉ። 

ሽማርሌዉ (ብረሃነ) ከደርግ ፅ/ቤት ከታሰረበት ወደ ማዕከላዊ ሲያመጡት የቀረዉ እስረኛ “ወደክፍላችሁ ግቡ! ብለዉ ሁሉም በየክፍሉ ሲመሽግ ታጅቦ የመጣዉን ቀይ መልከመልካም ልጅ ፊቱ በጥቁር ሪዝ ተከቦ፤ ጠጉሩም ረዥም በጥቅሉ ወደ ሇላዉ ተዘንፍሎ ገለጥ ብሎ የሚታየዉን ምንም ያልተሸበሸበዉን ግንባሩን፤ የደመቁት ቅንድቦቹንና ሽፋሽፍቶቹን አይተዉ “እሱ ማነዉ?” ብለዉ ሲጠይቁ ብርሃነመስቀል የኢህአፓዉ መሪ ይⶀቸዋል ፖሊሶቹ።

ከርመዉ እዚያ የእስር ቤቱ ኮሪዶር ዉስጥ ንፋስ ለመቀበል በተኮለኮልንበት የማዕከላዊ ኮሪዶር ስራዬ ብለዉ በአጠቀቤ ተቀመጡ።

ሲያወሩ ካቦዉ እንዳያያቸዉ እየተነጠቀቁ አፋቸዉን በጋቢያቸዉ ከልለዉ፤

“ታዱ አይዞሽ! ቀን ያመጣዉን መቻል ነዉ። ያልፋል፤ እስኪያልፍ ያለፋል እንጅ” አሉኝ።

“አዎን” ብቻ ብዬ ዝም አልኩ።

“እኔ እኮ ብርሃነመስቀል ሲባል ትልቅ አዛዉንት አድርጌ ነበር የምገምተዉ። ስሙ ሸምግሎ፤ እሱ ግን እንዲህ አንድ ፍሬ ነዉ? ይገርማል ለካ ዕድሜ ቇንቇ ነዉ!” አሉና ትንሽ ዝም ብለዉ በዙሪያቸዉ ያለዉን ቃኙና “እኔ እኮ ትላንት ነዉ ያየሁት” ብለዉ እዝን አሉ።

“ይገርⶁታል እኛም ሽማግሌዉ ነዉ የምንለዉ። በስም አንጠራዉም የሚወዱት የሚያከብሩት ሁሉ፤ እኔን ሚስቱን ጨምⶂ ሽማግሌዉ እንለዋልን” አልኯቸዉ።

“በትግል ዓላማማ ሸምግⶀል። የሱን ስም የማዉቅ ማን አለ? ትላንት እኮ ሲያስገቡት እነ ሽመልስ /የመዕከላዊ አዛዥ የሚሆኑት ጠፍⶆቸዉ ተናጡ እኮ! ምን ያድርጉ ጊዜ የሰጠዉ ቅል ድንጋይ ይሰብራል እንዲሉ”

እንዳሉትም እስረኛዉ ከተዘጋበት በሇላ በሩ ሲከፈትለት የሆነዉን እያጠያየቀ ‘ብረሃነመስቀል ነዉ’ ሰባት ቁጥር አስገቡት እየተባለ በሹክሹክታ ሲወራ እኔም ሰማሁ። ታድያ ለአንድ ሳምንት ይህል ከየክፍሉ ከላይ ቤት ታች ቤት ተቀባብሎ ተሰማማ። ልጅ አዋቂዉ በሚስጥር ሲጋራ ያለዉ ሲጋራዉን ሻይም ምግብም በሚስጥር ሰባት ቁጥር መላኩን ተያያዘዉ። ሰዉ የፍቅሩን ያህል እንዲያ ያድርግ እንጂ 7 ቁጥር ከአራቱ ክፍል አንዱ ክፍል ተዘግቶበታል። እኔና መኪያም መጀመሪያ እዛዉ ክፍል ነበር ወደ ሁለት ወራት የቆየነዉ።    

ሰባት ቁጥር ዉስጥ ሴቶች እኛ ብቻ በመሆናችን ጨለማ ዉስጥ በሩ ይዘጋብናል። ሶስቱ ወንዶች ያሉበት እያንዳንዱ ክፍል በር ክፍት ሆኖ እና ከሌላዉ እስረኛ ጋር የሚያገናኘዉ በር ግን ሁሌም ዝግ ነዉ። ጥላሁን ኪዳኔ፤ ዶክተር ካሳሁን መከተ እና አሰፋ ጫቦ ሶስቱ ክፍሎች ዉስጥ የነበሩት ናቸዉ።

የሰባት ቁጥር እሰረኞች ለመፀዳዳት እንኯ ሲወጡ በኮሪደሩ ግራና ቀኝ በትይዩ በተደረደሩት ክፍሎች ያሉት እስረኞች ወደ ክፍል እንዲገቡ ይታዘዛሉ።

ብረሃነመስቀልም ልክ እንደኛ ተቆልፎበት አንድ ሳምንት ብቻ ነዉ በማዕከላዊ የቆየዉ።

ሃሙስ፤ ሰኔ 29/1971ዓ/ም ከደርግ ፅህፈት ቤት አምጥተዉ ለአንድ ሳምንት ማከላዊ ካቆዩት በሇላ፡ በሃምሌ ስድስት ሃሙስ ከቅብኑ ሰባት ሰዓት አካበቢ ሽማግሌዉን ወሰዱት።  

ብረሃነ መዕከላዊ ከመምጣቱ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ በደርግ ፅ/ቤት ምርመራ ወቅት ስለኔ ሲጠየቅ፡ “እርⶃ ምንም አታዉቅም” በማለቱ እኔ ተጠርቼ ከእሱ ጋ ተመሳሳይ ጥያቄ አቀረቡልኝ። የኔም ምላሽ ከእርሱ የተለየ አለመሆኑን ካረጋገጡ በሇላ፡ ለጥቂት ደቂቃዎች ብቻችንን የመነጋገር እድል አገኘን። የለበሰዉ የወትሮዉን ሳርያን ኮትና ባቱ ላይ የሚቀር አጭር ተነፋነፍ ሱሪ ነዉ። ፀጉሩና ጢሙ አድጏል። አካሉ ተጎሳቁⶀል። የሆዴን መግፋት አስተዉሎ እጁን በመስደድ አይዳበሰ፡ “ታዲ ምን ላድርግሽ! አይዞሽ!” እያለ በሃዘን ተመለከተኝ። እኔም ስሜቱን ለማረጋጋት፡ “በህይወት ከቆየሁ ወንድ ልጅ ነዉ የምወልድልህ” ስለዉ ከነበረበት የሃዘን ድባብ ለአፍታም ቢሆን ወጥቶ፡ አይይ . . . እኔ እኮ ቀድሜም ነግሬሻለሁ። አንቺ 12 ብትወልጂ ሁሉም ሴት ነዉ የሚሆኑት” አለና በማዋዛት መለሰልኝ። ወዲያዉ ወታደረኦቹ መጥተዉ አለያይተዉ ወሰዱን። የዚያን ዕለት በቅርብ ተገናኝተን ጥቂት ቃላትንም ቢሆን መለዋወጣችን ሁልጊዜም ያፅናናኛል። በፅንስ ዕድገት ደረጃ ላይ ያለችዉን የመጨረሻ ልጁን በጣቶቹ ዳብⶃል። 

ያ የሃምሌ ስድስት ቀን ከሳምንቱ ቀኖች የተለየ ሆነ። የእኛ ቤቶች ምሳ ከመብላታችን በፊት ስድስት ሰዓት ላይ ወደ መታጠቢያ ቤት መሄድ የተለመደ ተራችን ነዉ።

ተሰልፈን ግራና ቀኝ ክፍሎችን እታማተርን በወንዶቹ ክፍሎች መሃል ስናልፍ የእኔ ዓይን ሰባት ቁጥር ላይ እንደተተከለ ነበር። አለወትሮዉ በሩ ገርበብ ብⶀል። ዶ/ር ካሳሁን መሬት ላይ ተቀምⶏል። ከሱ ሇላ ከለል ብሎ ብረሃነ /ሽማግሌዉ ይታያል። ቀጥ አልኩኝ። ወደፊት መራመድ አልሆነልኝም። እርሱም ዞር ብሎ አይቶኝ ኖሮ፡ በምልክት ጤንነቴን ጠየቀኝ። ደህና ነኝ እያልኩ በምልክት እየተነጋገርን ሳለ፤ ሳላስበዉ መቶ አለቃ ሽመልስ ከወደ ሇላዬ መጥቶ፡

እንዴ፤ እንዴ ምንድን ነዉ ታደለች? በማለት አቇረጠኝ። ምንም ሳልል ድንግጥ ብዬ መንገዴን ቀጠልኩ። ስመለስም በተበመሳሳይ ሁኔታ እንደገና አየሁት። ሳቅ ብሎ አይዞሽ ጠንክሪ የሚል የመበረታቻ ምልክት ሰጥቶኝ አለፍኩኝ። ‘የዚህ ቀን ክስተት አጋጣሚ ይሆን? ወይስ ሆን ብለዉ ኤእድንተያይ የፈለጉ የእስርቤት ሃላፊዎች ነበሩ? ሳንተያይ ቆይተን ዛሬ እንዴት ያለ ቀን ቢህን ነዉ የናፈቀኝን ፈገተታዉን የለገሰኝ፡ በምልክት አይዞሽ በርቺ መልዕክቱን ያስተላለፈልኝ? እስከወዲያኛዉ የተሰናበተኝ ቀን መሆⶈን ለማወቅ ግን ጥቂት ወራት መጠበቅ ነበረብኝ።

ምሳ እንደበላን ወዲያዉ ‘በየክፍላችሁ! የሚል አዲስ ትዕዛዝ መጣብን። ስንቅ አመላላሾች ብቻ ደጅ ሲቀሩ ሁላችንም በትይዩዎች ክፍሎቻችን ገብተን በሮቹ ተዘጉ።

እንደተለመደዉ “ሰዉ ሊወስዱ ነዉ. . . ሰዉ ሊወስዱ ነዉ በሚል ጉምጉምታ፡ ሁሉም በቀዳዳ እያሾለቆ ለማየት ሞከረ።

ትንፋሻችን እስኪሰማ ድረስ አካባቢዉ በፀጥታ ተዋጠ። ኮቴ መሰማት ጀመረ። በኮቴዎቹ መካከል ⶏⶏ የሚል የነጠላ ጫማ ድምፅ ተከተለ። በመኪያ ጀርባ ላይ ቆሜ በሽንቁሮቹ አⶐልቄ ለማየት ሞከርኩ። አልቻልኩም። ዝቅ ብዬ በቁልፉ ቀዳዳ ሳጮልቅ ብሩሃነን በጨረፍታ አየሁት። የመጨረሻ ምስሉን በጭንቅላቴ አስቀረሁ።

ከመአከላዊ ቢያንስ በየሳምንቱ አምስት . . . ሰባት. . . ወዘተ የኢሃፓ፡ የኤርትራ ነፃ አዉጪ ግንባር አባላት የተባሉ ሰዎች እየወሰዱ የዉሃ ሽታ ሆነዉ ቀርተዋል። አብዮት ልጆⶇን ትበላለች እንዲሉ በዚህ ሂደት ደርግ የራሱንም ካድሬዎች በሚስጥር ለመፍጀት አላመነታም።

የዚያን ዕለት ብርሃነመስቀልን ከመዕከላዊ፤ ዶ/ር ሃይሌ ፊዳን ከአራተኛ ክፍለጦር ዶ/ር ንግስት አዳነና ቆንጂት ከበደ ከከርቸሌ፤ የሃይማኖት መሪዎችን አቡነ ቴዎፍሎስንና ቄስ ጉዲናን ጨምሮ ቁጥራቸዉ ከሃያ በላይ የሆኑ ሰዎችን በዚያዉ ሰሞን ከየእስር ቤቶች ሰብስቦ፡ ደርግ ያለ ፍርድ ፈጃቸዉ።

“ለምን ነበር የብረሃነመስቀልን ስም ብቻ በመጥቀስ ‘ከአብዮቱ ወረንጦ ሊያመልጥ አይችልም በማለት ያወጁት? ለምንስ ነበር የትልቁን አብዮተኛ የሃይሌ ፊዳንም ሆነ የንግስት አዳነን ወይንም የሌሎቹን ስም ያላነሱት? ኢህአፓ በዚያን ጊዜ በአሲምባና በጎንደር ይንቀሳቀስ ስለነበር ብቻ ነዉ? ወይንስ ሌላ ምክንያት ይኖራል?” በማለት በዚያን ቀን ስለተደረገዉ ልፈፋ ከወርት በሇላ ስረዳ መጠየቅ ጀምሬ ነበር።

ስለዚህ ጉዳይ ከብዙ ዓመታት ቆይታ በሇላ ከዶ/ር እሸቱ ጮሌ ጋር ስንጨዋወት፤ ያገኘሁት መልስ የሚከተለዉን ነበር

“ብርሃነመስቀል ከመዉቃቸዉ ጥቂት ሰዎች ዉስጥ “larger than life” በሚለዉ መግለጫ ከሚታዉቁ ሰዎች አንዱ ነዉ። አንደበተ ርቱዕ፤ አስታዋይና ፌማ ሞገስ የታደለና ሃሳብ የማነጥፍበት ከዊዜዉ የቀደመ አብዮተኛ በመሆኑ ለስዙ ጊዜ የሚታወስ ነዉ። ኢሃአፓ ስህተቱን ተገንዝቦ እርማት ካደረገ ምን ያህል የሚያሰጋዉ ሃይል እንደሆነም እነ መንግስቱ ያዉቃሉ”። በዚህ ንግግር ዉስጥ ላቅ ያለ ስብዕናዉ ደርግን በተለየ ሁኔታ እንዲለፍፍ መስገደዱ ተገለጠልኝ። ሕይወት ተፈራም በመፅሃፍዋ “የብረሃነመስቀል መሞት የአንድ ዘመን ፍፃሜ መሰለ” በማለት ገልፃዋለች። 

ብርሃነመስቀልም ሆነ ሌሎች የለዉጥ ፈላጊ ትዉልድ አባላት በየድርጅቶቻቸዉ በማደራጀትና በመታገል ዉድ ጊዜያቸዉን በመጨረሻም ምትክ የሌለዉን ህይወታቸዉን ሰዉተዋል። አብዛኞቹ ዕድሜያቸዉ ገና አርባ እንኯን ያልሞላ ጎልማሶች ነበሩ። ብረሀነ ሲሞት 36-ዓመቱን ሊደፍን ሁለት ወራት ይቀሩት ነበር።

ሁል ጊዜ ቀድመዉ ነገሮችን የሚረዱ እንዳሉ ሁሉ፡ በአብዛኛዉ ቆየተዉ የሚረዱ ይበዛሉ። በአገራችን ቀድሞ ያወቀና የተረዳ ሰዉን እንደበጎ በመመልከት ከማድመጥ፡ አሳቡን ከመረዳትና ጫፍ ከማድረስ ይልቅ፡ ጎትቶ መጣል በበህላችን ይስተዋላል። ይህም በተረቶቻችንና በፅሁፎቻችን የሚገልጥ ነዉ። የፍቅር እስከመቃብሩን “ጉዱ ካሳን” እንደ አይነተኛ መገለጫ መወሰድ ይቻላል።

በማዕከላዊ ቆይታዬ የመጀመሪያዎቹን ሁለት ወራት ደርግ ፅ/ቤት እየተመላለስኩ ምርመራ ሲካሄድብኝ ብከርምም፡ ቀጣዮቹን አምስት ወራት ግን ያለምንም ፍርድ በማዕከላዊ እንድቆይ ሆነ። እርግዝናዬም እየገፋ ሲሄድ ምንም አይነት ህክምና ለማግኘት ባለመቻሌ፡ መቶ አለቃ ሽመልስ ወደ ከርቸሌ ብወርድ የተሻለ እንደሚሆን በማሰብ፡ የሰባት ወራት የመዕከላዊ ቆይታዬ እንዲያበቃ ምክንያት ሆነኝ።